Skip to main content

Posts

Showing posts from December 25, 2013

እሳት ወይ አበባ (ጸጋዬ ገብረ መድኅን)

ወንድ ብቻዉን ነዉ እሚያለቅስ ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ ተሸሽጎ ተገልሎ ተሸማቆ ተሸምቆ ከቤተ ሰዉ ተደብቆ መሽቶ የማታ ማታ ነዉ ሌት ነዉ የወንድ ልጅ እንባዉ ብቻዉን ነዉ የሚፈታዉ፡፡ . . . ብቻዉን ነዉ የሚረታዉ፡፡. . . . ችሎ ዉጦ ተጨብጦ ተማምጦ ተጣጥሮ በሲቃ ግት ተወጥሮ እንደደመና ተቋጥሮ እዉስጥ አንጀቱ ተቀብሮ . . . . መሽቶ፣ ረፍዶ፣ ጀምበር ጠልቆ የጨለማ ድባብ ወድቆ በእንቅልፍ ጥላ ሲከበብ፣ በዝምታ ሲዋጥ አገር ፍጡር ሁሉ ተስለምልሞ፣ ብቸኝነት ብቻ ሲቀር. . . . የኋላ ኋላ ማታ ምድር አገሩ በእፎይታ ዓይኑን በእንቅልፍ ሲያስፈታ ሁሉ በእረፍት ዓለምርቆ ብቸኝነት ብቻ ሲቀርብ ያኔ ነዉ ወንድ ዓይኑ የሚረጥብ የብቻ እንባ ወዙ እሚነጥብ፡፡ ብቻዉን ነዉ ብቻዉን ነዉ. . . . የእንባ ጨለማ ለብሶ ነዉ ወንድ ልጅ ወዙ እሚነጥበዉ፡፡ ዕጣዉን ብቻዉን ቆርሶ ብቻዉን ሰቀቀን ጎርሶ ብቻዉን ጭለማ ለብሶ ገበናዉን ሳግ ሸፍኖ ክብሩን በሰቆቃ አፍኖ ሌሊት የማታ ማታ ነዉ ሕቅ እንቁን እሚነጥበዉ ኤሎሄዉን እሚረግፈዉ. . . . ከዓይኑ ብሌን ጣር ተመጦ ከአንጀቱ ሲቃ ተቆርጦ ደም አልሞ ፍም አምጦ ከአጽመ-ወዙ እቶን ተፈልጦ እንደጠፈር-ብራቅ እምብርት እንደእሳተ ገሞራ ግት ‘ርቅ ነዉ ወንድ ልጅ እንባዉ ደም ነዉ ፍም ነዉ እሚያነነባዉ ንጥረ ሕዋስ ነዉ ሰቆቃዉ ረቂቅ ነዉ ምስጢር ነዉ ጣሩ . . .ብቻዉን ነዉ የሚፈታዉ ብቻዉን ነዉ የሚረታዉ፡፡ ችሎ ዉጦ ተጨብጦ ሰቀቀኑን በሆዱ አጥሮ በአንጀቱ ገበና ቀብሮ ዉሎ ጭጭ እፍን ብሎ እንደደመና ተቋጥሮ ጣሩን ዉጦ ተጣጥሮ በሲቃ ግት ተሰትሮ. . . . ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ ከቤተ-ሰዉ ተደብቆ አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ...