Skip to main content

እሳት ወይ አበባ (ጸጋዬ ገብረ መድኅን)


ወንድ ብቻዉን ነዉ እሚያለቅስ
ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ
አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ
ተሸሽጎ ተገልሎ ተሸማቆ ተሸምቆ
ከቤተ ሰዉ ተደብቆ
መሽቶ የማታ ማታ ነዉ ሌት ነዉ የወንድ ልጅ እንባዉ
ብቻዉን ነዉ የሚፈታዉ፡፡ . . .
ብቻዉን ነዉ የሚረታዉ፡፡. . . .
ችሎ ዉጦ ተጨብጦ ተማምጦ ተጣጥሮ
በሲቃ ግት ተወጥሮ
እንደደመና ተቋጥሮ
እዉስጥ አንጀቱ ተቀብሮ . . . .
መሽቶ፣ ረፍዶ፣ ጀምበር ጠልቆ
የጨለማ ድባብ ወድቆ
በእንቅልፍ ጥላ ሲከበብ፣ በዝምታ ሲዋጥ አገር
ፍጡር ሁሉ ተስለምልሞ፣ ብቸኝነት ብቻ ሲቀር. . . .
የኋላ ኋላ ማታ
ምድር አገሩ በእፎይታ
ዓይኑን በእንቅልፍ ሲያስፈታ
ሁሉ በእረፍት ዓለምርቆ ብቸኝነት ብቻ ሲቀርብ
ያኔ ነዉ ወንድ ዓይኑ የሚረጥብ
የብቻ እንባ ወዙ እሚነጥብ፡፡

ብቻዉን ነዉ ብቻዉን ነዉ. . . .
የእንባ ጨለማ ለብሶ ነዉ
ወንድ ልጅ ወዙ እሚነጥበዉ፡፡

ዕጣዉን ብቻዉን ቆርሶ
ብቻዉን ሰቀቀን ጎርሶ
ብቻዉን ጭለማ ለብሶ
ገበናዉን ሳግ ሸፍኖ
ክብሩን በሰቆቃ አፍኖ
ሌሊት የማታ ማታ ነዉ
ሕቅ እንቁን እሚነጥበዉ
ኤሎሄዉን እሚረግፈዉ. . . .
ከዓይኑ ብሌን ጣር ተመጦ
ከአንጀቱ ሲቃ ተቆርጦ
ደም አልሞ ፍም አምጦ
ከአጽመ-ወዙ እቶን ተፈልጦ
እንደጠፈር-ብራቅ እምብርት
እንደእሳተ ገሞራ ግት
‘ርቅ ነዉ ወንድ ልጅ እንባዉ
ደም ነዉ ፍም ነዉ እሚያነነባዉ
ንጥረ ሕዋስ ነዉ ሰቆቃዉ
ረቂቅ ነዉ ምስጢር ነዉ ጣሩ . . .ብቻዉን ነዉ የሚፈታዉ
ብቻዉን ነዉ የሚረታዉ፡፡

ችሎ ዉጦ ተጨብጦ ሰቀቀኑን በሆዱ አጥሮ
በአንጀቱ ገበና ቀብሮ
ዉሎ ጭጭ እፍን ብሎ እንደደመና ተቋጥሮ
ጣሩን ዉጦ ተጣጥሮ
በሲቃ ግት ተሰትሮ. . . .
ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ
ከቤተ-ሰዉ ተደብቆ
አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ
ተሸሽጎ ተከናንቦ ተሸማቆ ተሸማቆ. . . .
የብቻ ብቸኝነቱ የጭለማ ልብሱ እስኪደርስ
በዓይን አዋጅ ሃሞቱ እንዳይረክስ
ቅስሙ በገበያ እንዳይፈስ
ተገልሎ በእኩለ-ሌት ወንድ ብቻዉን ነዉ እሚያለቅስ፡፡
Source:- የግጥም ምሽት በፌስቡክ https://www.facebook.com/groups/189373957880006/

Comments

Popular posts from this blog

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የዓለም ሊቀ ሊቃውንት፣ የኪነ ጥበብ ምሑር የተከበሩ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ (ጥቅምት ፲፫ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ/ም- ሚያዝያ ፪ ቀን ፳፻፬ ዓ/ም)፤ ‘’ኪነ ጥበብ የሰው ልጅን መንፈስ ለማዳበር፣ ሀገራችንን ለማሳደግ፣ ለማሳወቅ እና ለሕይወታዊ ኑሮ ተስፋ ለመፍጠር የላቀ ሚና ይጫወታል’’ ይላሉ። ለጥቀውም ‘’ዛሬ የምንሠራው ሥራ የዛሬን ሕይወት እያንጸባረቀ ለነገው ትውልድ ፈር መቅደድ አለበት፡፡” በሚል ስሜት ኪን ማንኛውንም የሰው ኑሮ ረገድ የሚነካ እንደሆነ ያስረግጣሉ። በዓለም የታወቁና የተከበሩት ኢትዮጵያዊ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌ በሰሜን ሸዋ በምትገኘው የሸዋ ነገሥታት ከተማ አንኮበር ላይ ጥቅምት ፲፫ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ/ም ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ተወለዱ። ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ፋሺስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በግፍ ሲወራት፣ የልጅነት ትዝታቸውም ይሄው የግፍ ወረራ እና ጦርነት የሚያስከትለው የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ፤ ከነጻነትም በኋላ ዐቢዩ ሥራ በወረራ የተበላሸችውን ሀገራቸውን እንደገና መገንባት እንደሆነ ነው። ለዚህም የሀገር ግንባታ አስፈላጊውን እውቀት መሸመት የፈለጉት በ ማዕድን ምሕንድስና ዘርፍ ነበር። ወላጆቻቸውና ዘመድ አዝማዶች ግን የኪነ ጥበብ ስጦታቸውን በቤታቸውና በከተማው ዙሪያ በሚስሏቸው ስዕሎች ተገንዝበውት ነበር። የመጀመሪያና መካከለኛ ትምህርታቸውን የት እና መቼ እንዳጠናቀቁ የተጻፈ መረጃ ባናገኝም፤ ገና በአሥራ አምስት ዓመታቸው በ ፲፱፻፵ ዓ/ም ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው የምሕንድስና ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ እንግሊዝ አገር ይላካሉ። ተሰዳጅ ተማሪ ወጣቶቹ ንጉሠ ነገሥቱን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሲሰናበቱ፣ አፈወርቅ ተክሌ ጃንሆይ የ...

When one loves nature and all its value, art takes the position to tell the story!

ፍቅር በአርጩሜ! ያኔ ትምህርት ቤት ቀለሙን ስንቀልም፣ ስሌት ስናሰላ ሰይንስ ስንጠበብ፣ አይናችን ሲገለጥ ሁሉን ስንካን፣ ፍቅርን ዝም አሉን የኛ መምህር፡፡ ትዝ ይለኛል ያኔ.... የክፍሌ ተማሪ ፍቅር ብታሲዘኝ፣ አይናፋርነጸቷ ዝምታዋ ቢያመኝ፣ ፍቅረሯ አያማለለ መማሩ ቢሳነኝ፣ ትዝ ይለኛል ያኔ.... ቃላት አውጣጥቼ ደብዳቤ መፃፌ፣ ባማሩ ቃላቶች ወደድኩሽ ማለቴ፤ ግና ምን ይሆናል.... ወድጃለሁ ብዬ ሃሳቤን በገለፅኩ፣ እሰልፉ መሃል ላይ ባርጩሜ ተገረፍኩ፡፡ መቼ በዚህ ብቻ.... እንደወንጀለኛ ፍርድ እንዳጎደለ፣ ማፍቀሬ ተወራ ጉድ እየተባለ፡፡ መቼ በዚህ ብቻ.... የአርጩሜው መዘዝ ስር አየሰደደ፣ ፍቅር በአርጩሜ ከኔ ተዋሀደ፡፡ ይመስገነው ዛሬ ሴትን አልጠይቅም፣ የማፍቀሩን ፀጋ ነፃነት አላውቅም፣ ሰጠየቅ እሺ እንጂ እኔ አልጠይቅም፡፡ እኔ!?.... ምን በወጣኝ! - እኔ አልጠይቅም፣ እኔ!?.... በስመአብ!! - እኔ አልጠይቅም፣ እኔ!?.... እማማ ትሙት - እኔ አልጠይቅም፡፡ 1981 ዓ.ም. — ናዝሬት በመስፍን ገብሬ ወንዳፍራሽ (ቅንጣት 2005 ዓ.ም.)

ትናንት 05/04/2006 ዓ.ም.የግጥም መድብል ....

አስገራሚ ገጠመኞች የተስተዋሉበት የግጥም መድብል ምርቃት ትናንት 05/04/2006 ዓ.ም. በልዩ ሁኔታ በኢትዮጲያ  ወመዘክር አዳራሽ ተፈፀመ፡፡