Skip to main content

አሁንም መጠየቅና መጠየቅ አለብን!!!

የትራንስፖርት አገልግሎቱ እንዳይሻሻል እንሻለን?!

 እኔ ሀገር እየኖራችሁ ስለትራንስፖርት ችግር ሳትሰሙ እና ሳታወሩ መዋል እና ማደር ከቶ እንደማይቻል የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በሁለቱም ገዢዎቻችን  (በሙሰኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና በህጋዊ ማእቀፍ በህገወጥነት ከሚበለፅጉት ነጋዴዎች) ዘንድ የመፍትሄ ሀሳብ ሊቀርብበት የተደፈረ ጉዳይ እንኳ አልመስል ብሏል፡፡

የመኪና መንገዶች
አብዛኛው አስፋልት መንገድ ከፈሰሰበት የሀብት መጠን አንጻር በበርካታ ምክኒያቶች ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጥ እንደሚቀር ከሁሉ አይን የተሰወረ ባይሆንም፣ መልካም አስተዳደር ጉድለት ግን ችግሩን አባብሶታል፡፡
እኔ ተዘዋውሬ በማውቅባቸው ቦታዎች ሁሉ ያስተዋልኩት አንዱ ነገር የመኪና ማቆም (ፓርኪንግ) ነው፡፡ የቀለበት መንገዶችን ጨምሮ (ለብዙ የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፖች እንዳልተመረጡ …. ጊዜ ጥሏቸው…) በርካታ የአስፋልት መንገዶች በህጋዊና በህገ-ወጥ መንገድ የፓርኪነግ አገልግሎት ለመስጠት ብቻ የተሰሩ ይመስላሉ፡፡ በርካታ ጎሚስታዎችና ጋራዦችም ስራቸውን በተቀላጠፈ መንገድ የሚያከናውኑት በእነዚህ በከፍተኛ ወጪ በተገነቡ  አስፋልት መንገዶች ላይ ነው፡፡
አንዳንዱ መንገድ ላይማ በግራም በቀኝም መኪኖች ተኮልኩለው ቆመው ታክሲዎችም ሆኑ የአደጋ ጊዜ አምቡላንሶች በስቃይ ጩኸት እየታገሉ የእንፉቅቅ ርጀም ጊዜ ፈጅቶባቸው እንደሚያልፉ አላየንም ብሎ ሊክድ የሚችል ነዋሪ አይገኝም፡፡ እነዚህን ቁጭቶች በገንዘብ ስሌት ቀይረን ብናያቸው ነገሩን የተሸለግልፅ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ ….... ለምሳሌ አንዲት ኮብል ንጣፍ መንገድ ዳር የሚቆምን አነስተኛ ርዝማኔ ያለው ተሸከርካሪ ምን ያህል ገንዘብ ላይ ቆሞ እንደሚውል እናስላ፡፡ (ቪትዝዎን መትረው አብረውን ያስሉት!)
ያን ሰሞን በኢቲቪ ለዜና ማሟያ ቃለ-መጠይቅ ሲደረግላቸው ከነበሩ ኮብል ድንጋይጠራቢዎች አንዱ ከሃያ እስከ ሰላሳ ፍሬ የኮብል ድንጋይ ለማምረት የሚያስችለውን ፍላጭ ከብር ሃምሳ እስከ ሰማኒያ ገዝቶ ያመረተውን የኮብል ፍልፍል በነፍስ ወከፍ ከብር 2.50 እስከ 4.00 እንደሚያጣራ ተናግሮ ነበር፡፡ ንጣፉ ሲሰራም ስምሪት ሚወጡ የመንገድ ግንባታ ከባድ መኪኖች፣ ልምድ ያላቸውና የሌላቸው መሀንዲሶች፣ ሙሰኛ የዘርፉ አማካሪዎች እና የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ተቆጣጣሪዎች መደበኛ ክፍያዎችን ወጪ መጠየቁ መዘንጋት የለበትም፡፡
አንዲት የኮብል ንጣፍ ፍልፋይ ድንጊያ ደግሞ 10 ሳሜ ወርድ እና 10ሳሜ ስፋት ያላት ካሬ መሆኗበይፋ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ አንድ አነስተኛ ርዝማኔ ያለውን ተሸከርካሪ ለማቆም ቁጥራቸው ከ450 እስከ 600 የሚደርሱ ፍልፋይ/ጥርብ ድንጋዮችን የፈጀ የቆዳ ስፋት ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱትን አንዳንድ ተጨማሪ ወጪዎች ከግምት በማስገባት በገንዘብ ስንተምነው ደግሞ  ይህን አነስተኛ መኪና አቁሞ ለሚሄድ ሹፌር ከአስር ሺህ ብር ያላነሰ ወጪ የተደረገበት የኢትጲያን ሀብት እያባከንክ ነው ብሎ መገሰፅ ተቆርቋሪ ዜጋ መሆናችንን ያሳያል፡፡ የአስፋልት መንገድ ግንባታና ጥገና ወጪ ደግሞ የዚህን ስንትና ስንት እጥፍ እንደሆነ መናገገር ለቀባሪው እንደ ማርዳት ነው፡፡
(እናንተ የመንገዱን የአገልግሎት ዘመን ከግምት በማስገባት በቀን ከዚያ መንገድ የሚሰበሰበውን የ ፓርኪነግ ገንዘብ ጋር አነፃፅሩት!)

የሾፌሮች ስነምግባር
በማህበረሰባችን ውስጥ የነበረው ከፍተኛ የመከባበር ባህል በአስደንጋጭ ሁኔታ መቀየሩ በርካቶችን የሚያሳዝን ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ አለመከባበር እንዲሰፍን ከሚያደርጉ ተፅዕኖዎች ጥቂቶቹ ጉንጭ አልፋው የመንግስት በአፋጣኝ ችግሮችን የመፍታት ባህሪን ጨምሮ፤ የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ መግበት፤ አድልዎ፣ ጉቦኝነት፣ የግንዛቤ ችግር (እውቀት ማጠር/ ማይምነት)፤ … ወዘተ… ሲሆኑ በመኪና መንገዶቻችን ላይ የሚስተዋለው የሾፌሮች ባህሪ ግን በከፍተኛ ዝቅጠት ላይ እንዳለን የሚያመላክት ነው፡፡
ቅድሚያ ለእግረኛ የማይታሰብ ነው፡፡ (እርግጥ የእግረኛ መንገዶች ብዛትም፣ ጥራትም የሌላቸውና ብርቅ በመሆናቸው ምክኒያት እግረኛውም፣ እንስሳውም፣ የጎዳና ላይ ንግዱም፣ ጎርፉም፣ ሆነ ሌላው የሚደባደቡት የመኪናውን መንገድ ለማጣበብ ነው፡፡) መስቀለኛም ሆነ የውስጥ ለውስጥ መታጠፊያ መስመሮች ላይ የሚገናኙ መኪኖች ከቤተ እምነት ወይም ከሲኒማ ሚወጡ ታደሚ ይመስል ትከሻ ለትከሻ ሳይገጫጬ መተላለፍ የማይታሰብ ነው፡፡ ሁሉ እኔ እቀድም ባይ ነው! ….
የታክሲ ሾፌሮች ከሚኮሩበትና ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ዘወትር ከሚነጋገሩበት ጉዳይ ዋንኛው ትርፍ መጫንና ትርፍ ማስከፈል ናቸው፡፡ (መሽቷል፣ ዝናብ ነው፣ ፀሐይ ነው፣ መንገድ ተዘጋግቷል፣ ነዳጅ የለም፣ ሰልፍ ላይ ያለው ሰው አያሳዝንም ወይ፣ ሒሳቡ እኮ አያዋጣም፣ ለተራ አስከባሪ 50/80 ብር ነው የከፈልነው፣ …ወዘተ የረዳቶች የዘወትር ቋንቋ ነው፡፡) በሕግ አስራ አንድ ሰው ለመጫን የተፈቀደለትመኪና አስራ ስምንት እና ሃያ ሰው ማጎር “ዘጭ ነው!” ይባልለታል፡፡ የአራት ብሩን የታክሲ ሰልፍ አስር ብር ቢያስከፍሉም በወረፋና በድብድብ የምናገነው እድል እንደሆነ እኛ ተሳፋሪዎች በደንብ እናውቃለን፡፡
የትራፊክ ደህንነት ምርመራን ሳያልፉ ዓመታዊ የስራ ፈቃዳቸው እንደማይታደስ ብናውቅም፣ ቤቀኑ የሚገጥሙን መኪኖች እና እውቀት በሌለን ተሳፋሪዎች አይን እንኳ ከሰላሳ አስከ መቶ የቦሎ/ ክላውዶ መታደስን ሚያስነፍጉ ችግሮችን ልናወጣለቸው የሚችሉ ተሸከርካሪዎችን በየቀኑ እናያለን፡፡ ግን ማንም አይሰማንም፡፡ እነዚህ መነኪኖች ግን ከአቅማቸው በላይ ህዝብን እንደ ልባሽ ጨርቅ ጠቅጥቀው ጭነው በተፈቀደላቸው እና ባልተፈቀደላቸው የከተማ መንገዶች ላይ እንደ በርሜል የሚንከባለሉ ይመስል በመምዘግዘግ በግድ የለሽነት እየነጠሩ እና እያነጠሩ ይሾፈራሉ፡፡

ላዳዎች (ሜትርታክሲዎች)
ከስራ ሰዓታቸው ይልቅ የመቆሚያ ሰዓታቸው ሚበዛው ትንንሾቹ የከተማ ታክሲዎች አገልግሎት ከጥንቱ ሰማያዊና ነጭ ቅብ ላዳዎች እስከ ቢጫ ቀለም ሜትር ታክሲዎችን የሚያጠቃልል የታክሲ አገልግሎት ምድብ ነው፡፡ ትንሹ በላዳ (ሜተር ታክሲ) የመጓጓዣ ዋጋ ስልሳ ብር ሲሆን አነስተኛ ሻንጣ ከያዙ ደግሞ ብር መቶ ያስከፍላል፡፡ ይህ ዋጋ ለመደበኛ ታክሲ ተጓዦች በአንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ወጪ የሚሸፈን ነው፡፡ (አርባ/ ስልሳ ሰባት እጥፍ … ለምቾት!)  ከሁለት እስከ ሶስት የታወቀ ፌርማታ ለመጓዝ ያለሻንጣ ብር መቶ ሃምሳ ከሻንጣ ጋር ከሆነ ደግሞ ብር ሁለት መቶ እና ከዚያ በላይ ይከፍላሉ፡፡ (የመደበኛው የታክሲ ክፍያ ዋጋ አራት ብር ከሃምሳ መሆኑን ልብ ይበሉ፡፡) መደበኛ የታክሲ ተሳፋሪዎች ትረፍ ከፈልን ብለው የሚያማማርሩበትን የአስር ብር መንገድ የለሻንጣ በላዳ/ ሜትር ታክሲ ቢጓዙ የኢትዮጲያ ብር ሶስት መቶ መክፈል ግዴታዎ ነው፡፡ ሻንጣዎ ዳጎስ ያለ ከሆነ ደግሞ ሌላ ሁለት መቶ ብር እላዩ ላይ ጣል ያደርጉበታል፡፡ (መልካም መንገድ!)
በ2008 ዓም መጨረሻ አካባቢ ወደ ስራ የገቡትና በከተሜው አጠራር “የውበት እስረኞች” ሚባሉት ቁጥራቸው ከስምንት መቶ የሚበልጡ ሜትር ታክሲዎች በረዥም ጊዜ የባንክ ብድር ክፍያ እና ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ የተሸለ አገልግሎት በተመጣጠነ ዋጋ ለደንበኞች ለመስጠት ሲባል ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገ ነው፡፡
ሆኖም መንግስት በኪሎሜትር ከተጠቃሚ እንዲሰበስቡ የተፈቀደላቸው ብር አስር ከመንገዱ መጨናነቅና የነዳጁን ዋጋ መዋዠቅ ተከትሎ አዋጭ ስላይደለ በብር አስራ አንድ ከሃያ ሳንቲም አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ እንዲፈቅድ ማህበራቱ በመጠየቃቸውና የዚህ ምላሽ በመንግስት በኩል በአግባቡ ባለመሰጠቱ ከስምምነት አልደረስንም በሚል አሳማኝ ያልሆነ ምክኒያት በብዙ የመንግስት ድጋፍ ወደ ሀገር የገቡት ታክሲዎች ያለፉትን ሁለት ዓመታት ዘረፋ ሊባል በሚችል መልኩ ከላይ በተገለፀው  የጉዞ ክፍያ ዋጋ በሚያገኙት ገቢ እየተዳደሩ ነው፡፡ 

ተራ አስከባሪዎች
በታወቁና ባልታወቁ ፌርማታዎች ተሳፋሪዎችን ጠብቀው እንዲሳፈሩና ታክሲዎቹም እንደየአመጣጣቸው በተራቸው እንዲስተናገዱ የሚያደርጉት አስተዋፅዖ ይሄ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን ለእነዚህ ተራ አስከባሪዎች የሚከፈለውን ገንዘብተ ከትሎ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ለሚነሱ ተደራራቢ የክፍያ ጭማሪዎችና አግባብነት ጋር በተሳፋሪው ዘንድ የሚነሱት ቅሬታዎች ጥቂት አይደሉም፡፡
መገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ ላምበረት፣ ቃሊቲ፣ አየርጤና፣ አውቶቡስ ተራ፣ መርካቶ፣ ቦሌ፣ ፒያሳ፣ መከኒሳ፣ ጀሞ፣ አለም ገና፣ቄራ ወይም ሳሪስ ያሉ ፌርማተዎችን ብቻ ብንታዘብ፣ በቀን የትየለሌ ገንዘብ በጥቂቶች የገንዘብም ሆነ ንብረት አስተዳደር እውቀት የሌላቸው ወይም ከፍተኛ የሱስ ተጋላጭ በሆኑ ወጣቶች እጅ ይሰበሰባል፡፡ (ሰርቶ ለመሸታ ቤት ማለት ነው!) ለምሳሌ አንድ ሚኒባስ ታክሲ ከመገናኛ ቃሊቲ ተራ ጠብቆ ጭኖ ሲወጣ ለተራ አስከባሪዎቹ በአዘቦት ቀናት የኢትዮጲያ ብር ሃምሳ ይከፍላል፡፡ (በባዕል ቀናት እና አመሻሹ ላይ ከሆነ ደግሞ ብር ሰባ ወይም ሰማኒያ ይከፍላል፡፡)  በሁለቱ ፌርማታዎች ጫፍም በትንሹ በቀን በድምሩ ከሁለት መቶ እስከ ሶስት መቶ ብር ከአንድ ሚኒባስ ታክሲ ይቀበላሉ፡፡ (የባዕል ቀናቱንና የምሽቱን ሒሳብ እናንተ አስሉት!) እነዚህ ወጣቶች ስራ ፈጣሪነታቸው ቢያኩራራቸውም ህይወታቸው ሲቀየር አይታይም፡፡ በሁለቱም ፌርማታዎች የሚሰሩት ተራ አስከባሪዎች ቁጥር ተደምሮ አስር የማይሞላ በመሆኑ፣ በቀን መቶ ሚኒባስ ታክሲዎች ከተመላለሱ ከሃያ ሺህ እስከ ሰላሳ ሺህ የሚሆን የኢትዮጲያ ብር የሰበሰበውን ቡድን አባላት ወርሃዊ ገቢ በደሞዝ ስሌት ያለ ግብር በነፍስ ወከፍ ከብር አርባ አምስት ሺህ እስከ ብር ስልሳ ሺህ መሆኑን አለማወቅ ተገቢ አይሆንም!

የትራፊክ ፖሊሶች
ሕግ ማስከበር መቼም በየትኛውም ሀገር ቀላል ስራ ሆኖ አያውቅም፡፡ ብቃት ያላቸውና በቁጥርም በርካታ የሆኑ ሰራተኞች ከሌሉ ደግሞ ጫናው እጅግ እንደሚበዛ ግልፅ ነው፡፡ በመዲናችን የሚታየው ግን ትንሽ ግር ያሰኛል፡፡ በቡድን ስብስብ ብለው ጥላ ስር የሚቀመጡ የትራፊክ ፖሊሶችን ማየት አያስገርምም፡፡  ለምን ቢሉ የጀበና ቡና በመጠጣት ሰበብ በአንገብጋቢ የስራ ሰዓት ሳይቀር በየካፌው የሚታዩ የትራፊክ ፖሊሶች ሞልተዋል፡፡
ግን ዋናው ነገር ይሄ አይደለም፡፡ ወጥ የቅጣት ሂደት ቤመኪናው መንገድ አናይም፡፡ ያዝ ለቀቅ ደግሞ ከሕጉ የበላይነት ጋር መናናቅን ያመጣና ይልቁንም የትራፊክ ፖሊሶችን ለይስሙላ ያህልም ቢሆን ያስከብራቸዋል፡፡ (ያው ጥቅማ ጥቅም ካስገኘላቸው ተከበሩበት ወይም ከበሩበት ማሰኘቱ አይቀርማ!) እንዲያውም በርካታ የመስመር እና የከተማ ታክሲ ሾፌሮች ተሰባስበው እቁብ ይጥሉላቸዋል ይባላል፡፡ (የሾፌሮችም አሉባልታ ከሆነ…. እናንተ አጣሩ!) ሕጉን በታማኝነት ማስከበር ብንችልበት ኖሮ፤ ወጥ አሰራር ባላቸው ድርጅቶች ቀርቶ የግለሰብ ቤቶች እንኳ ሁሉ ስርዓት ይዞ የድርሻውን ኃላፊነት የሚወጡ ዜጎች የሚበራከቱበት ይሆን ነበር፡፡

እናሳ?
ታዲያ ምን ተሸለ? ለማን አቤት ይባል? የትራንስፖርት ማኔጅመንት ፅፈት ቤት ምን እየሰራ ነው? ሁሉም እንደየ አቅሙ ከደሃው ያለአግባብ የሚሰበስበው ገንዘብ እንደ ሀገር ኪሳራ አያስከትልም? ኪሳራውን ማስላት ባይቻል፣ ግፍ አይሆንብንም? ደሃ ቢጠፋ እኮ ባለጠጋው መነፃፀሪያ ያጣል! የነገው ሀብታም ራሱን ከማን ጋር አነፃፅሮ ደህንነት ይሰማዋል?

እስኪ ሀሳብ ስጡበት!
*** *** *** *** *** *** *** *** *** *** ***
የመወያያ ነጥቦች
·         ታክሲው ሁሉ የጂፒኤስ መከታተያ እና መቖጣጠሪያ ቢገጠምለት?
-          የስራ ሰዓት ቁጥጥር እና ግምገማ
-          የመጫን አቅም ቁጥጥር
-          የጉዞ/ ስምሪት መስመር ክትትልና ቁጥጥር
·         የውስጥ ለውስጥ የሰፈር መንገዶች ባለ አንድ አቅጣጫ/ ዋን ዌይ ቢደረጉ?
·         የትራፊክ ምልክቶችን መተካት የኢንሹራንስ አማራች ቢኖር?
·         ልዩ ቦታ ካልተዘጋጀ/ ላይ ባይ/ በቀር በዋና ዋና መንገዶች ላይ ለጥገና፣ ጎሚሰታ፣ እጥበት፣ ፓርኪነግ አገልግሎቶች ማቆም ከፍተኛ ቅጣት ቢያስከትል?
·         ድንገተኛ የትራፊክ ደህንነት ምርመራ ተደርጎባቸው የማይመጥኑ መኪኖችን ሲያሽከረክሩ መገኘት ለእስር እና ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ቢያስከትል?

Comments

Popular posts from this blog

ትናንት 05/04/2006 ዓ.ም.የግጥም መድብል ....

አስገራሚ ገጠመኞች የተስተዋሉበት የግጥም መድብል ምርቃት ትናንት 05/04/2006 ዓ.ም. በልዩ ሁኔታ በኢትዮጲያ  ወመዘክር አዳራሽ ተፈፀመ፡፡

ቀልድ ስላለማወቃችን

12/11/2006EC አንድ ሰሞን ወደሁለት ተከፍላ ብዙም ሳትቆይ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የገባችው ሱዳን የገጠማትን ምስቅልቅል ሁኔታ ለመከታተል አለም ሁሉ ጆሮውን አቁሞ ነበረ፡፡ ቀድሞም ጠግቦ ያላደረው ደሃ ሕዝብ ነፍሱን ስለማቆየት ሲል ወደጎረቤት ሀገራት ተሰዷል፡፡ በዛ አስቸጋሪ ወቅት ግን አቶ ሳልቫኪየር ከየሀገራቸው እድገትና ስልጣኔ ያልተመጣጠነ ምቾት ስላሰከራቸው አቻዎቻቸው ጉዳይ እንጂ ስለ ሕዝባቸው ፈፅሞ ግድ የሌላቸው እንደሆነ መሰከሩልን፡፡ “የፀጥታውን ስምምነት የፈረምኩት የኢትዮጲያው ጠቅላይ ሚኒሰተር አስርሃለሁ ስላሉኝ ነው”-ብለው አስደመሙን፡፡  ጋዜጠኞቹም ለጉዳዩ መልስ ሲጠባበቁ ቆዩና ሰሞኑን አቶ ኃይለማሪያምን ማብራሪያ ይጠይቋቸዋል፡፡ እርሳቸውም ሳልቫኪየር ቀልዴን ነው ብለዋል ሲሉ መለሱ፡፡ እንዲያውም እነዚህ ጋዜጠኞች ቀልድ አያውቁም ብለው መናገራቸውን ሊያብራሩ ሞክረው አለፉ፡፡ ይህም የአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ደረቅ ቀልድ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ኢቴቪ 1 ፣ 2 ፣ 3 ፣ 4 ተብሎ ይቀለዳል፤ ስለመብራት ስርጭት ብዙ ቁም ነገር የሚመስሉ ቀልዶች እንሰማለን፤ እናያለን፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ላይ በተጠናከረ መልክ እየሰሩ መሆኑን ይነግሩናል__የቀልዳቸውን፡፡ መንግስት ጸረ - ሰላም ሀይሎች የህዝብን ጥቅም የሚነኩ ኢ - ሰብዐዊ ድርጊቶችን ለመፈጸም ሲያሴሩ ደርሼባቸዋለው ብሎ የቀልዱን ይነግረንና አሴሩ የተባሉትን አሳራቸውን ያበላቸዋል፤ግን የቀልዱን ነው፡፡የሃገሪቷን ሰላም ለማደፍረስ ስለመነሳታቸው መረጃ የለማ ! ቀላል የከተማ ባቡር መጓጓዣን ስራ ለማሰጀመር ሩጫው እየተፋጠነ መሆኑ በተደጋጋሚ በቴሌ...

ናዝሬትዬ መሪዎችሽ ለምን ይፈሩሻል?

Tesfaye Waktola https://www.facebook.com/twaktola Andinet Ada-nazreth ናዝሬትዬ መሪዎችሽ ለምን ይፈሩሻል? ድሮም ጃንሆይ ናዛሬት/አዳማ መምጣት አይወዱም ነበር፣ይባላል፡፡በዚህም የተነሳ ለገላውዴዎስ ት/ቤት መሰረትና ምርቃት ከመምጣታቸው ውጪ ሌላ ጊዜ መች እንደመጡ ሲነገርም አልሰማሁም፡፡መንጌም ሲመጣ በጣም ተደብቆና በድንገት ሲሆን ፣የማስታውሰው ለናዝሬት ቴክኒክ ኮሌጅ (የዛሬው አዳማ ዩኒቨርሲቲ) መሰረትና ምርቃት መምጣቱን ነው፡፡ከዚያ በተረፈ ሁለቱም መሪዎች ወደ ሶደሬ ሲያልፉ ረዥም እድሜ ተመኙ ተብሎ ሕፃናት ወጥተን ቪቫ (VIVA JANHOY! …viva mengistu!..)ብለን እንገባ ነበር፡፡ያኔም ድንገት ካየናቸው ደስታችን ወሰን የለውም ነበር፡፡የልጅ ነገር!ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እጫወት ነበር …ያለው ማነው? ታዲያ ፍርሃት የተጋባበት መሌም ናዝሬት መጣ ከተባለ ከተማው በፌደራል ይወረራል፡፡ከዚያ የት እንዳደረ ሳይታወቅ ወይ ምሽቱን ሄዷል ወይ …አድሯል፡፡ካደረ ጎብዟል፡፡ግን መሌ ሶደሬ ሄዶ ያውቃል?….ቢዚ ስለነበር ምስኪን፣…. ግን ግን-ሶስቱም መሪዎችሽ ለምንፈሩሽ- ---እውነት ግን አዳማ/ናዝሬትን ለምን ፈሯት…? እስቲ እኔ ልገምት፡፡ ጊዜው በጣም ሩቅ ነው ይባላል፡፡ዓጼ ገላውዴዎስ ከግራኝ ጋር ጦርነት ገጥመዋል፡፡ጦርነቱ ተፋፍሞ ዓጼው ብዙ ከገፉ በኋላ ግራኝ ጦሩን አስተባብሮ እየገፋ ይመጣል፡፡ይሄኔ ላለመማረክ ሲዋጉ የነበሩት ንጉስ በስተመጨረሻ ይቆስላሉ በኋላም አሁን ካለው ከዓጼ ገላውዴዎስ ከፍ ብሎ ካለው ከአለሌ ወንዝ ማዶ ባለ ቦታ ተገድለው ተገኙ፡፡በኋላም ግራኝ አንገታቸውን ቆርጦ ወደ ሃረር ወስዶ በግንቡ ላ ሰቀለው የሚል ዲስኩር በገላውዴዎስ ት/ቤት ግቢ ውስጥ በ 50ኛ ...