12/11/2006EC
አንድ ሰሞን ወደሁለት
ተከፍላ ብዙም ሳትቆይ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የገባችው ሱዳን የገጠማትን ምስቅልቅል ሁኔታ ለመከታተል አለም ሁሉ ጆሮውን አቁሞ
ነበረ፡፡ ቀድሞም ጠግቦ ያላደረው ደሃ ሕዝብ ነፍሱን ስለማቆየት ሲል ወደጎረቤት ሀገራት ተሰዷል፡፡ በዛ አስቸጋሪ ወቅት ግን አቶ
ሳልቫኪየር ከየሀገራቸው እድገትና ስልጣኔ ያልተመጣጠነ ምቾት ስላሰከራቸው አቻዎቻቸው ጉዳይ እንጂ ስለ ሕዝባቸው ፈፅሞ ግድ የሌላቸው
እንደሆነ መሰከሩልን፡፡ “የፀጥታውን ስምምነት የፈረምኩት የኢትዮጲያው ጠቅላይ ሚኒሰተር አስርሃለሁ ስላሉኝ ነው”-ብለው አስደመሙን፡፡
ጋዜጠኞቹም ለጉዳዩ መልስ
ሲጠባበቁ ቆዩና ሰሞኑን አቶ ኃይለማሪያምን ማብራሪያ ይጠይቋቸዋል፡፡ እርሳቸውም ሳልቫኪየር ቀልዴን ነው ብለዋል ሲሉ መለሱ፡፡ እንዲያውም
እነዚህ ጋዜጠኞች ቀልድ አያውቁም ብለው መናገራቸውን ሊያብራሩ ሞክረው አለፉ፡፡ ይህም የአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ደረቅ ቀልድ ሆኖ
ተመዝግቧል፡፡
ኢቴቪ 1፣2፣3፣4 ተብሎ ይቀለዳል፤ ስለመብራት ስርጭት ብዙ ቁም ነገር የሚመስሉ ቀልዶች እንሰማለን፤ እናያለን፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ላይ በተጠናከረ መልክ እየሰሩ መሆኑን ይነግሩናል__የቀልዳቸውን፡፡ መንግስት ጸረ-ሰላም ሀይሎች የህዝብን ጥቅም የሚነኩ ኢ-ሰብዐዊ ድርጊቶችን ለመፈጸም ሲያሴሩ ደርሼባቸዋለው ብሎ የቀልዱን ይነግረንና አሴሩ የተባሉትን አሳራቸውን ያበላቸዋል፤ግን የቀልዱን ነው፡፡የሃገሪቷን ሰላም ለማደፍረስ ስለመነሳታቸው መረጃ የለማ!
ቀላል የከተማ ባቡር መጓጓዣን ስራ ለማሰጀመር ሩጫው እየተፋጠነ መሆኑ በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን የተገለጸው__ ቀልድ፤ እንዲያውም በቀልዱ መዘዝ ተነጠፈ የተባለው
ሀዲድ ተመልሶ ሲፈታ በአይናችን በብረቱ አይተናል፡፡
ስለደሞዝ
ጭማሪ በርካታ ጊዜ ፓርላማ ለሚሰበሰቡ ተወካዮች እና በቴሌቪዥን እና ሬድዮ ለሚከታተሉ ዜጎች እንደማሽላ እያሳረሩ የሚያስቁ ንግግሮችን የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስተር አቶ መለስ ያደርጉ ነበር፡፡ ቀልደኛ ነበሩ፡፡ የእርሳቸውን ሞት ተከትሎም በፓርላማ መቀመጫ 2 ቁጥር የተጻፈባትን ጠረጴዛ እያሳዩ ማንም በፓርላማው ላይ ሊቀልድ እንደማይችል__ ይህም ለሃዘኑ መባባስ መግለጫ ቁም ነገር ሆኖ በተደጋጋሚ ሲቀለድ ነበር፡፡
በሰሞንኛው የቴሌቪዥን ዲስኩር ደግሞ የመንግስት ሰራተኞችን ደምወዝ ጭማሪ መነገር አስመልክቶ የዋጋ ማስተካከያ ላደረጉ ወይም ለሚያደርጉ ነጋዴዎች ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ__ ቀልድ እየተነገረ ነው፡፡ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል የሚባል ቀልድ፣ ዋና ዋና አስመጪዎች፣ ዋና ዋና አጓጓዦች፣ ዋና
ዋና ደላሎች፣ ዋና ዋና ተቆጣጣሪዎች፤___ ግን አይቀልዱም፡፡ለምን መንግስት እንደሚቀልድ በደንብ ያውቃሉ፡፡ በደንብ ይመሳጠራሉ፡፡ የመጨረሻ ተጠቃሚ
ደግሞ እየማቀቀና እየተቀለደበት ይሞታል፡፡
መንግስታችን ቀልድ ስለሚወድ ኢኮኖሚውን የሚቆጣጠረው የቀልዱን ተገቢ ጥናት እንዳደረገ እየነገረን በዘፈቀደ እና በድንገት
በሚወስደው እርምጃ ነው፡፡ ለምሳሌ፡ የዛሬ ሶስት አመት አካባቢ የዶላር ምንዛሬ ዋጋ በአንድ ጊዜ 13 ብር ወደ 16 ብር ከፍ አለ፡፡
ከማግስቱ ጀምሮ ቀስ ቀስ እያለ እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በቁሳቁሱ ሁሉ ላይ ታየ፡፡ በዚህም ዶላርን በአይኑ አይቶ የማያውቅ የኔ ቢጤ ደሃ ህዝብ እጅግ የተሻሻለ ድህነትን ይለማመድ ዘንድ ተፈረደበት፡፡
እርሱንም በጸጥታ ያጣጥማል፡፡
አሁንም የመንግስት ሰራተኛው ደሞዝ ድንገት በ100% ወይም በ150% ሊያድግ እንደሚችል እየተሰማ ነው፡፡ ይህ ቀልድ
አይደለም__ ይከፈላል፡፡ ነገር ግን ቀልዱ አግባብነቱ ላይ ነው፡፡ የታሸገ ውሃ፣ ስኳር፣ ዘይት፣ አልባሳት፣ የምግብ ቤቶች ዋጋ
ሁሉ በአንድ ጊዜ 100% እና 150% እንዳልጨመረ ግልጽ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ጭማሪውን ተከትሎ የሚኖር የሸቀጥ ዋጋ ልዩነት ላይ
ከፍተኛ ቁጥጥር ተደረገ አልተደረገ ለውጥ የለውም፡፡
በንግድ ዘርፉ ውስጥ በተለያየ ደረጃ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች እንደመንግስታችን ስለማይቀልዱ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸን አደጋ
ላይ አይጥሉም፡፡ ቀስ ቀስ እያሉ በየሳምንቱ እና በየወሩ ሁኔታዎችን እያመቻቹ ዛሬ በመካከለኛ ምግብ ቤቶች ከ45 ብር እስከ 90
ብር የሚሸጠውን ጥብስ ከአንድ እና ሁለት አመት በኋላ ከ120ብር እስከ 180 ብር ሊያደርሱት አይችሉም ይባላል?___በፍፁም!___እነርሱ
እንደመንግስታችን አይቀልዱማ፡፡
ሳሙና ከ3 ብር 14 ብር የገባው በአንድ ጊዜ አልነበረም፡፡ ዳቦ ከ20 ሳነቲም ወደ 1 ብር ከ40 ሳንቲም፤ ቢራ ከ2
ብር ከ70 ሳንቲም ወደ 13 ብር፤ ወተት ከ2 ብር ወደ 12 ብር የሻቀቡት በአንድ ጊዜ ባይሆንም አስር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ
የእያንድንዳቸው ዋጋ ከ200% እስከ 600% ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ደሞዝ ግን የዚህን የሩብ ሩብ አልጨመረም ነበር፡፡__አያችሁ
ቀልድ?! የሰሞኑ ጭማሪ እሙን ቢሆን እንኳ እጅግ የዘገየ የቀልድ ጭማሪ ነው፡፡
የት/ቤቶች ክፍያ፣ የትራንስፖርት፣ የመዝናኛ ቦታዎች ዋጋ እንኳ በፍፁም ከእነዚህ ሊወዳደር አይችልም፡፡ ድሮ ከኢዲስ
አበባ ናዝሬት ስትሄዱ ከለገሀር ተነስታችሁ የአዳማ ከተማ መነሀሪያ በአማካይ ከ 1፡30 አስከ 2፡00 ያህል ጊዜ ይወስድባችኋል፤
6 ብር ለትራንስፖርት ይከፍላሉ፡፡ ዘንድሮ ግን በጉዞዎ ከ 3፡00 እስከ 4፡00 ያባክናሉ/ይባክንብዎታል፤ ለዚህም እስከ 42 ብር
ለትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ይከፍላሉ፡፡
ናዝሬት መጥተው ደግሞ ሶደሬ ጎራ ማለትዎ አይቀርምና ቀድሞ 3 ብር የነበረው የትራንሰፖርት ክፍያ ወደ 15 ብር ከፍ
ብሎ ይጠብቅዎታል፡፡ የመግቢያ ክፍያው ደግሞ ጥቂት ጭማሪ ብቻ ተደርጎበት ከ5 ብር ወደ 41 ብር ከፍ ብሏል፡፡አይስክሬም ከ 3
ብር ወደ 18 ብር፣ የታሸገ ውሃ ደግሞ ከ 15 ብር እስከ 25 ብር በሆነ ዋጋ ያገኛሉ፤ ሌላውን በአካል ሄዶ መታዘብ የእርስዎ
ድርሻ ነው፡፡
“ቀልዱን ተይ” የሚለው የማን ዘፈን ነበረ? ሀገር ግን እንዴት በቀልድ ልትመራ ትችላለች? ለምን የቀልድ ጥናቶች፣ የቀልድ
እሰሮች፣ የቀልድ ሞቶች፣ የቀልድ ሀውልቶች፣ የቀልድ ትምህርቶች፣ የቀልድ የሲቪል ማህበራት፣…ወዘተ፣ ይበዛሉ? ቀልድ ስላለማወቃችን
መነገር የለበትም ታዲያ?...የቀልድም ቢሆን! የሆነ ትምህርት ስለቀልድ መማር አይኖርብንም? ሳናውቀው ህዝብ ላይ ስንቀልድ እነዳንገኝ
ይጠቅመን እነደሆነ?...!!!
Comments
Post a Comment