(This post had been originally posted on April 03,2013 on my other blog please consider the original date)
በርካታ ባህላዊና ዘመናዊ መንግስታትን ያለ ግልፅ ቅኝ ተገዢነት ያስተናገደችው ሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የመልካም አስተዳደር እጦትና የሰበዓዊ መብት ረገጣ እየተባባሰ በመምጣቱ ሳቢያ ሕዝቡ የዜግነት መብቱን በመንግስት ስልጣን ላይ ባሉ ግለሰቦች ወይንም ቡድኖች ፈቃድ ብቻ ሊሰጠው ወይም ሊነፈገው የሚችል መሆኑን እያመነ መጥቷል፡፡
ይባስ ብሎ መንግስት ለሕዝቡ ጥቅም በሚል በሚዘረጋቸው በማንኛውም የልማት መርሀ ግብሮች የመንግስትንና የግል ሌቦችን በሚያበረታታ መልኩ በዘፈቀደ አሰራር እየተሰራ ነገር ግን ለይስሙላ ያህል የሒሳብና የሚዲያ ሪፖርቶች እንደሚደረጉ ያደባባይ ሚስጥር ከሆነ እየሰነበተ ነው፡፡
የሆኖ ሆኖ ለሃያ አመታት፤ ሊያውም በዚህ በዘመነ ግሎባላይዜሽን ሀገራችንን በስልጣን ሲያስተዳድር የቆየው ኢሕአዴግ ከስልጣን ጊዜው ቀድሞ የክፉውን ጨለማ ሳይቀር አሸንፎ የመጣለትን ጠንካራ (በእኔ አተያይ አስሊ እና ከዱረዬ ባልተናነሰ በፈንግጪው ውጤት ተኮር) የሆነ መሪውን ካጣ ይኸው መንፈቅ ሞላው፡፡ ያለአንድ አምባገነን ምልክትነት ሕዝቡን ሰቅዞ ይዞ መምራት ያለመደበት የኢትዮጲያ መንግስት አገዛዝ ቀጣዩን መሪ አይነኬ አድርጎ በህዝቡ ላይ ለመሳል ተስኖት እየተውተተረተረ ይገኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እነዳለም የመለስን ፋውነዴሽን ለማቋቋም ጥረቱ ቀጠሎ በመጪው ቅዳሜ በይፋ ፀድቆ ስራ ይጀምራል፡፡
የቅርቡን ቢልከሊነተንን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት መሪዎች፤ ታዋቂ አረቲሰቶችና በየተለያዩ ስራቸው እውቅናና ሀብትን ያተረፉ የየዘርፉ ባለሙያዎች ራሳቸው እነደ አምባሳደር በመሆነን በርካታ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን የሚሰሩ ድርጅቶችን አቋቁመው በአካባቢ ማህበራዊ እና ስነ-ምህዳራዊ ፋይዳዎችን ለማሻሻል ሲተጉ ይስተዋላል፡፡
ምንም እንኳ እኔ በግሌ የአቶ መለስ አድነናቂ ባልሆንም በረካታ የአፍሪካ፤የአውሮፓ፤ የእስያና የአሜሪካ ባለስልጣናትና ባለሀብት ወዳጆች እንደሚኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ እንኳን ሙስና በተስፋፋበትና ሀገሪቱ በአንፃሩ የሰላም ችግር የሌለባት ጊዜ ለሃያ አንድ ዓመታት የመሩተ እሳቸው ይቅርና በፋሽስት ዘመን ወረራ የደረሰባቸው አፄ ኃ/ስላሴ እና በኢትዮጲያ የእርስ በእርስ ጦርነት ዘመን አምባገነን መሪ የሚል ስም የተለጠፈላቸው ጓድ መንግስቱ ኃ/ማሪያምም ቢሆኑ በመከራቸው ጊዜ ለሊሸሽጋቸው የሚችሉ ወዳጆችን በሹመት ዘመናቸው አፍርተው ነበር፡፡
ስለሆነም በአቶ መለስ ስም ለሚቋቋመው ፋውነዴሽን በረካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ዜጎችና ድርጅቶች ገንዘባቸውን ሊሰጡና ፖለቲካዊ፤ ሐይማኖታዊ ወይም ሌላ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚችሉበትን መንገድ የበጁ እንደሆነ ጥረት ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
ግና የዚህ ፋውንዴሽን ዓላማ የግለሰቡ መልካምነት መወደሻ መሆኑ ቀርቶ ለኢሕአዴግ መደነሻ፤ የልማት ሰራዎች አጋር መሆኑ ቀርቶ የተቀናቃኝ ፓረቲዎች መግረፊያ አሳር ከሆነ ፋውንዴሽንነቱ ይቀርና ይፈነደሳል፡፡
ነገር ግን የህ ፋውንዴሽን አቶ መለስ ነበራቸው ተብሎ የሚታመንበትን ከፍተኛ የንባብ ልምድ ለተተኪው ትውልድ የሚያስተላልፍበትን ሰፊ ፐሮጀክተ የቀረፀና የሚሰራ ከሆነ፤ ሀይለቃልን ሳይቀር በበሰለ ቋንቋ እየተጠቀመ ተቀናቃኙን በትህትና መርታት የሚችል አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ ማፍራት የሚችልን መድረክ ካዘጋጀ፤ እንደቆሎ በተለቀመ እጅፅሁፍ አካሄዶችንና መመሪያዎችን መንደፍ ማዋቀርና ማብራራት የሚችሉ ፀሃፍትን የሚመለምልበት መንገድ ከቄሰ፤ እውነትም የሰውውን ስም ለዘመናት ማወደስ የሚችል ማዕከል የሆንና በሕይወት ዘመናቸው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወይም አቅም በማጣት ያከናወኗቸውን የግፍ ተግባራት ያሰተሰርይላቸዋል፡፡
ልናይ ኋላ ዶሮ “ለጄ ጭራም አትበላ፤” ብላለች አሉ፡፡
Comments
Post a Comment